እንግሊዝ እና ጣልያን ለሴቶች አውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ ዛሬ ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
እንግሊዝ እና ጣልያን ለሴቶች አውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ ዛሬ ይጫወታሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/ 2017 (ኢዜአ)፦ በ14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር እንግሊዝ እና ጣልያንን ያገናኛል።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በጄኔቭ ስታዲየም ይካሄዳል።
የወቅቱ የውድድሩ የዋንጫ ባለቤት እንግሊዝ በሩብ ፍጻሜው ስዊድንን በመለያ ምት 3 ለ 2 በማሸነፍ አራት ውስጥ ገብታለች።
እንግሊዝ ስዊድንን ያሸነፈችበት መንገድ ከወቅቱ የዋንጫ ባለቤት የሚጠበቅ አይደለም የሚል ትችት አስተናግዳለች።
በጨዋታው ለረጅም ደቂቃዎች 2 ለ 0 ስትመራ ቆይታ በጨዋታው መገባዳጃ ላይ ያስቆጠረቻቸው ግቦች ከውድድሩ ከመሰናበት አትርፏታል።
ተጋጣሚዋ ጣልያን በሩብ ፍጻሜው ኖርዌይን ባልተጠበቀ ሁኔታ 2 ለ 1 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በአውሮፓ ዋንጫ መድረክ ተገናኝተው አያውቁም። ይሁንና በአጠቃላይ በውድድር እና ወዳጅነት ጨዋታዎች 30 ጊዜ ተገናኝተዋል።
ጣልያን 15 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ እንግሊዝ 9 ጊዜ ድል ቀንቷታል። 6 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ካደረጉት ያለፉት ስድስት የውድድር ጨዋታዎች መካከል ጣልያን አምስት ጊዜ ስታሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
በጨዋታው እንግሊዝ የስብስቧ ጥልቀት እና የስነ ልቦና ጥንካሬ ጨዋታውን እንድታሸንፍ እድል ይሰጣታል ቢባልም በጠንካራ የራስ መተማመን ላይ የምትገኘው ጣልያን ጠንካራ ፍልሚያ ታደርጋለች።
በጨዋታው የእንግሊዝ አጥቂ ክሎዊ ኬሊ እና በሩብ ፍጻሜ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረችው የጣልያኗ የፊት መስመር ተሰላፊ ክርስቲያና ጂሬሊ ይጠበቃሉ።
አማካይ ክፍል ላይ የእንግሊዟ ጆርጂያ ስታንዌይ እና የጣልያኗ አሪያና ካሩሶ ቡድናቸው ብልጫ እንዲወስድ የሚያደርጉት ፍጥጫ ትኩረትን ስቧል።
የእንግሊዝ እና ጣልያን አሸናፊ በፍጻሜው ከጀርመን እና ስፔን አሸናፊ ጋር ይገናኛል።
የ39 ዓመቷ ክሮሺያዊ ኢቫና ማርቲኒች የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ትመራለች።