የኢትዮጵያን የማንሰራራት ብስራት ለዓለም እያስተዋወቀ የሚገኘው ኪን ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ቡድን በቤጂንግ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የማንሰራራት ብስራት ለዓለም እያስተዋወቀ የሚገኘው ኪን ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ቡድን በቤጂንግ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2017(ኢዜአ)፦ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውና የኢትዮጵያን የማንሰራራት ብስራት ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ የሚገኘው ኪን ኢትዮጵያ የባህልና የኪነ ጥበብ ቡድን በቻይና ቤጂንግ ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
ኪን ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ቡድን የኢትዮጵያን የማንሰራራት ብስራት ለዓለም ለማስተዋወቅ እየሰራ ይገኛል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ቡድኑ የኢትዮጵያን ቱባ ባህሎች፣ ሙዚቃዎች፣ አለባበሶች፣ የፋሽንና ዲዛይን ውጤቶች፣ የሰርከስ ትርዒቶች፣ የቡና ስነ ስርዓትን የተመለከቱ ትዕይንቶች በቻይና የተለያዩ ከተሞች ያቀርባል ብለዋል።
ኪነ ጥበብ የኢትዮጵያና ቻይና የቆየ ዲፕሎማሲያዊና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከር የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሌሎች ሀገራትና ተቋማት ጋር አጋርነት በመፍጠር ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ኪን ኢትዮጵያ የባህልና ኪነ ጥበብ ቡድን የኢትዮጵያን የማንሰራራት ብስራት ለዓለም ለማስተዋወቅ ሚናው የላቀ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ናቸው።
ኪን ኢትዮጵያ የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ግንኙነቶች የበለጠ ለማጠናከር ያግዛል ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው የኪን ኢትዮጵያ የባህልና ኪነ ጥበብ ቡድኑ ለዲፕሎማሲ ስራ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
ኪን ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብና ባህል ቡድን በቻይና ቤጂንግ ለአንድ ሳምንት በመቆየት የኢትዮጵያን የማንሰራራት ብስራት ለቻይናውያንና ለሌሎች ሀገራት ዜጎች የሙዚቃና የተለያዩ ትርዒቶችን በማቅረብ እንደሚያስተዋውቅ የኢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።
በኪን ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብና ባህል ቡድን የሁሉንም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የወከሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መሳተፋቸውም ተገልጿል።