ለመጅሊስ ምርጫ ስኬታማነት የዑለማዎች ሚና ከፍተኛ ነው- ሼይኽ ሱልጣን አማን - ኢዜአ አማርኛ
ለመጅሊስ ምርጫ ስኬታማነት የዑለማዎች ሚና ከፍተኛ ነው- ሼይኽ ሱልጣን አማን
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2017(ኢዜአ)፦ለመጅሊስ ምርጫ ስኬታማነት ዑለማዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼይኽ ሱልጣን አማን ገለጹ።
በአዲስ አበባ መጅሊስ አዘጋጅነት ከተማ አቀፍ የዑለማ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼይኽ ሱልጣን አማን፣ የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ መሪዎችና ዑለማዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተለያዩ የመወያያ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼይኽ ሱልጣን አማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት የመጅሊስ ምርጫ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በእስልምና እምነት ዑለሞች ያላቸው ቦታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪዎቹን በነጻነት የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም የዑለሞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን እና ለዚህም የመሪነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሲካሄድ የነበረው የመራጮች ምዝገባ ትናንት መጠናቀቁን ገልጸው ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ዑለሞች ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ሼይኽ ሁሴን በሽር በበኩላቸው በጉባኤው ከሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የተውጣጡ የዑለማ አባላት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
የጉባኤው አላማም በቀጣይ በሚካሄደው የምርጫ ስራዎች ላይ መወያየት መሆኑን ጠቁመው ዑለማዎች ህዝበ ሙስሊሙን በማንቀሳቀስ ረገድ ሰፊውን ድርሻ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ሼይኽ የአቁብ ሙሀመድ መሰል መድረኮች ለዑለማዎች እንዲሁም ለህዝበ ሙስሊሙ ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በነሐሴ ወር የሚከናወነው የመጅሊስ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅም የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ለምርጫው ስኬት የሚያደርጉት ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ሼይኽ ሸምሰዲን ባዴ ጉባኤው ሚናቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።