በመላ ሀገሪቱ 63 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በመላ ሀገሪቱ 63 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 14/2017(ኢዜአ)፦በመላ ሀገሪቱ 63 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ክንውን እና የ2018 ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሀዋሳ ከተማ እየተወያየ ነው።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ በተሰሩ ሥራዎች በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት እመርታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል።
ዘርፉን ለማጠናከር በተሰሩ ሥራዎች የተጠቃሚዎች ቁጥር በእማዎራና አባዎራ ደረጃ ወደ 13 ነጥብ 67 ሚሊዮን መድረሱን ጠቁመው፣ በቤተሰብ አማካይ መጠን ሲሰላም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር 63 ሚሊዮን እንደሚጠጋ አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በበጀት ዓመቱ 15 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መዋጮ ከጤና መድህን አባላት እና ከክልሎች የተናጥል ድጎማ ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡
እንደ ሀገር ከ4 ሺህ 300 በላይ ከሚሆኑ ጤና ተቋማት ጋር ውል በመግባትም ለማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።
እነዚህ ተቋማት የውስጥ አሰራራቸውና አቅማቸውን በማጎልበት ለተጠቃሚዎች የተሻለ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የስድስት ወር ቅድመ ክፍያ ቀድመው እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ሰላማዊት መንገሻ (ዶ/ር) ባለፉት አምስት ዓመታት የጤና መድህን አገልግሎት ሥራን ከነበረበት ዝቅተኛ አፈጻጸም ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በእነዚህ ዓመታት በክልሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ዜጎች መጠን ከ18 በመቶ ወደ 72 በመቶ ለማሳደግ መቻሉን የገለጹት ኃላፊዋ፣ በዚህም ከ2 ሚሊዮን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
መዋጮ መክፈል ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ የክልሉ መንግስት ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈሉንም ሰላማዊት (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሀኑ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት አንድ ሚሊዮን 219 ሺህ አባዎራና እማዎራዎች ውስጥ 889 ሺህ የሚሆኑት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ከእነዚህ ተጠቃሚዎች በአጠቃላይ 807 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ጠቁመው የገቢ አቅምን መሠረት ያደረገ የአከፋፈል ስርአት መኖሩ የተሻለ ገንዘብ ለመሰብሰብ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በ104 ወረዳዎችና ከተሞች የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን ለመክፈት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ናፍቆት፣ በአሁን ወቅት 37ቱን ሰርቶ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል ብለዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚቆየው መድረክ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡