በመዲናዋ በተጠናቀቀው በጀት አመት የወንጀል ምጣኔን በመቀነስ ስኬታማ ተግባር ተከናውኗል- ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት አመት በመዲናዋ ህብረተሰቡን የጸጥታ አካል በማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ወንጀልን በመከላከል ስኬታማ ስራ መከናወኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የ2017 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸምን እየገመገመ ነው፡፡


 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በግምገማ መርኃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ወንጀልን ቀድሞ መከላከል የፖሊስ ዓቢይ ተግባር ነው፡፡

ወንጀሎች ተፈጽመው ሲገኙ ወንጀል ፈጻሚዎችን ተከታትሎ በቁጥጥር ስር በማዋል የህግ የበላይነትን ማረጋገጥም ሌላኛው ተልዕኮ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ጠቅላይ መምሪያው ወንጀሎችን በመከላከል እና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

የጠቅላይ መምሪያው ወንጀልን የመከላከል አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው በዚህም በከተማዋ ይፈጸሙ የነበሩ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ወንጀሎችን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

የ2017 በጀት አመት ወንጀልን የመከላከል አቅም ከ2016 በጀት አመት ጋር ሲነጻጻር የ18 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ውጤቱ የተገኘው ህብረተሰቡን የጸጥታ ስራው አካል ማድረግ በመቻሉ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ጠቅላይ መምሪያው ወንጀልን የመከላከልና የምርመራ ስራውን ማዘመን መቻሉና ከባለድርሻ አካላት ጋር የነበረው ቅንጅታዊ ስራ ለተገኘው ውጤት የራሱን ድርሻ ማበርከቱን እንዲሁ፡፡

የህብረተሰቡን ሰላም በአስተማማኘኝ ሁኔታ ከማረጋገጥ በተጨማሪ የአደባባይ በዓላት፣ አህጉራዊ እና አለማቀፋዊ መድረኮች ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄዱ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በወንጀል መከላከልና በምርመራ ስራው ከህብረተሰቡ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

 ዛሬ በተጀመረው የግምገማ መድረክ ከመዲናዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የፖለስ ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም