ቀጥታ፡

ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳለጠ መልኩ ለማካሄድ የሕግ ማሻሻያ ተደርጓል - የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳለጠ ሁኔታ ለማካሄድ በሕግና አሰራር ላይ የነበሩ ክፍተቶች እንዲሻሻሉ መደረጉን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ገለፁ።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ተሻሽሎ የፀደቀውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን አስመልክተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ቦርዱ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ የሚያስችለውን የቅድመ-ዝግጅት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ የሕግ ክፍተቶችን ማሻሻል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ቦርዱ ላለፋት ስድስት ዓመታት ሲሰራበት የነበረውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ እንዲሻሻል ማድረጉን አመልክተዋል።

በማሻሻያ አዋጁ በርካታ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውንና 26 ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀድሞ አዋጅ ምርጫን ለማስፈፀም በምርጫ ጣቢያና ምርጫ ክልል ላይ የሚመድባቸው ምርጫ አስፈፃሚዎች በቂ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተሻሻለው አዋጅ እንደምርጫ ጣቢያዎቹ ሁኔታ አስፈፃሚ የሚመደብበት አሰራር መኖሩን ገልጸው፤ አዋጁ የቅሬታ አቀራረብ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን እንዲያርም ተደርጎ መሻሻሉንም አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል አንድ ዜጋ 18 ዓመት ካልሞላው ለመራጭነት መመዝገብ እንደማይችል አስታውሰው በተሻሻለው አዋጅ ግን መራጩ በምርጫ ቀን 18 ዓመት የሚሞላው ከሆነ መመዝገብ እንዲችል ተደርጓል ብለዋል።

በተመሳሳይ ዕጩዎችም በምርጫ ቀን 21 ዓመት የሚሞላቸው ከሆነ መመዝገብ እንዲችሉ ተደርጓል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የድጋፍ ፊርማ ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሻሻሉን ነው ሰብሳቢዋ ያብራሩት።

በዚህም ቀደም ሲል የሴቶችና አካል ጉዳተኞችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ይጠየቅ የነበረው የድጋፍ ፊርማ እንዲቀንስ ተደርጎል ብለዋል።

በቀደመው አዋጅ በምርጫ የሚሳተፋ የመንግስት ሰራተኞች ለምርጫ ዝግጅት ያለደመወዝ እረፍት እንደሚሰጣቸው አስታውሰው፣ በተሻሻለው አዋጅ ሰራተኞቹ ከደመወዛቸው ጋር እረፍት እንዲሰጣቸው መደረጉን አንስተዋል።

በተሻሻለው አዋጅ የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ እንዲሁም ብሄራዊ መታወቂያን መጠቀም እንዲቻል መደረጉንም አንስተዋል።

ይሁንና የብሄራዊ መታወቂያው አስገዳጅ የሚሆነው ለዕጩዎች ብቻ ሲሆን እንደ ሁኔታው መታወቂያ ሊጠየቅባቸው የሚችሉ አሰራሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው ሁለተኛ አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ አዋጅን ማፅደቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም