መከላከያ ሰራዊታችን የኢትዮጵያ ኩራትና የሰላማችን መከታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሰራዊታችን የኢትዮጵያ ኩራትና የሰላማችን መከታ ነው
ጅማ፤ሐምሌ 14/2017(ኢዜአ)፡-መከላከያ ሰራዊታችን የኢትዮጵያ ኩራት፣የሰላማችን አለኝታና መከታችን ነው ሲሉ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በመከላከያ ሰራዊት የዳሎል ዕዝ ዓመታዊ ኮንፈረንሱን አስመልክቶ የሰራዊቱ ማርሽ ባንድ በጅማ ከተማ ደማቅ ትርኢት አሳይቷል።
የከተማው ነዋሪም ትርኢቱን የተመለከተው ሲሆን መከላከያ ሰራዊታችን የኢትዮጵያ ኩራትና የሰላማችን መከታ ነው ብሏል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ተስፋዬ ረታ በሰጡት አስተያየት፥ መከላከያ ሰራዊታችን የሀገር አለኝታ በመሆኑ እንኮራበታለን ሲሉ ገልጸዋል።
ሰራዊቱ የሀገርን ሉአላዊነትና የአካባቢውን ሰላም የሚያስከብር ፣ የሕብረተሰቡ አለኝታ መሆኑን አንስተዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ከሊፋ አባፊጣ፥መከላከያ ሰራዊታችን የሉአላዊነት ምልክታችን ነው፤ ሰላምን ያስከብራል፤ሕዝቡን ይጠብቃል ሲሉ ተናግረዋል።
ከሕብረተሰቡ ጋር በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ስራ አብሮነቱን እያሳየ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በመከላከያ ሰራዊት የዳሎል ዕዝ የሰራዊቱ የስነልቦና ግንባታ ሀላፊ ኮሎኔል ለቺሳ መገርሳ በበኩላቸው፥ዕዙ ከመደበኛው ተግባሩ በተጓዳኝ ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን በተለያዩ የልማት ተግባራት ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።
በማህበራዊ አገልግሎት የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በመከወን አብሮነቱን ሲገልጽ መቆየቱን አንስተው፤ የማርሽ ባንድ ትርኢቱም ሕዝባዊ አጋርነትን ለመግለጽ ያለመ ነው ብለዋል።
በዕዙ የተዘጋጁት የተለያዩ ኩነቶች ሰላምን እና የሕብረተሰብ አብሮነትን የሚያጎሉ ጉዳዮች መሆናቸውንም አንስተዋል።
ዛሬ የዕዙ አጠቃላይ እንቅስቃሴ የተመለከተ ኮንፍረንስ በጅማ እንደሚካሄድ ተመልክቷል።