ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 10 ሜዳልያዎችን በማግኘት አጠናቀቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 10 ሜዳልያዎችን በማግኘት አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/ 2017 (ኢዜአ)፦ በናይጄሪያ አቡካታ ከሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ሶስተኛው የአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የመዝጊያ ቀን በተደረጉ የፍጻሜ ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳልያ አግኝታለች።
ከ18 ዓመት በታች 5 ሺህ ሜትር ሴቶች ርምጃ ፍጻሜ አትሌት ሕይወት አምባው በማሸነፍ ለኢትዮጵያ በውድድሩ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች።
አትሌት ኤልሳቤጥ አማረ ከ18 ዓመት በታች 800 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር አንደኛ በመውጣት አሸንፋለች።
ከ20 ዓመት በታች 800 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ሲሳይ አለቤ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳልያ አግኝቷል።
ውጤቶቹን ተከትሎ ኢትዮጵያ ሁለት የወርቅ፣ ሶስት የብር እና አምስት ነሐስ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን አግኝታ ውድድሩን ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።