የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አቅጣጫው በቱሪዝም ዘርፉ አዳዲስ መዳረሻዎችና ለሰው ሀብት ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል - ኢዜአ አማርኛ
የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አቅጣጫው በቱሪዝም ዘርፉ አዳዲስ መዳረሻዎችና ለሰው ሀብት ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2017(ኢዜአ)፦ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አቅጣጫው በቱሪዝም ዘርፉ አዳዲስ መዳረሻዎችና ለሰው ሀብት ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በመጀመሪያ ዲግሪና በደረጃ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምርቃት ስነ-ስርዓቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አቅጣጫው በቱሪዝም ዘርፉ አዳዲስ መዳረሻዎችንና ለሰው ሃይል ልማት ስራ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዚህም በቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት፣ በሰው ኃይል ግንባታ፣ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን በማስፋት እንዲሁም በሌሎች በርካታ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡
ተመራቂዎች በተማሩባቸው የሙያ ዘርፎች ለሀገራቸው ዕድገትና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም አሳስበዋል፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ስልጠናዎቹን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ያሟሉ ለማድረግ በርካታ የምርምርና ጥናት ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አሻራቸውን በማሳረፍ ላይ የሚገኙ በርካታ የሰለጠነ የሰው ሀብት ማፍራቱን ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት ለ57ኛ ጊዜ ተማሪዎችን ማስመረቁን ጠቁመው ከተመራቂዎቹ መካከልም አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከተመራቂዎቹ መካከል አሸናፊ ደገፋ እና ሳሙኤል ጥበቡ እንዳሉት፤ በተማሩበት የሙያ መስኮች መንግስት በሚያከናውናቸው የቱሪዝም ልማቶች ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ባገኙት የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ዕውቀት ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በማስተዋወቅ በኩል የበኩሏን ለመወጣት መዘጋጀቷን የገለጸችው ደግሞ የቱር ጋይድ ተመራቂዋ አያንቱ አለማየሁ ናት፡፡