ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን እውን ለማድረግ በሚሰራው ሥራ ከወጣቱ የላቀ አስተዋጽኦ ይጠበቃል-ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 13/2017(ኢዜአ)፦ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን አልምቶ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን እውን ለማድረግ በሚሰራው ሥራ ከወጣቱ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚጠበቅ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳደሯ ከወሰን ተሻጋሪ የበጎፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ጋር ዛሬ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በጋምቤላ ከተማ አካሂደዋል።


 

ርዕሰ መስተዳደሯ በዚሁ ጊዜ እንደክልል ብሎም እንደ ሀገር የብልጽግና ጉዞን ማሳካት የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩን ተናግረዋል።

በየአካባቢው ያሉትን የተፈጥሮ ጸጋዎች በማልማት የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ለማረጋገጥ መንግስት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር እየተከናወኑ ባሉ የልማት፣ የሰላምና የአብሮነት ግንባታ ሥራዎች ወጣቱን በማሳተፍ የታለመውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳደሯ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በየአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማት የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ወጣቱ ግንባር ቀደም ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ለሀገር ልማትና እድገት ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ወይዘሮ አለሚቱ፣ ወጣቶች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች  ሁሉ ለሰላም ግንባታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከወሰን ተሻጋሪ የበጎፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች መካከል ወጣት ተመስገን ማርቆስ በሰጠው አስተያየት መነሻቸውን ከአፋር ክልል አድርገው እያከናወኑት ባለው የበጎፈቃድ አገልግሎት ሥራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግሯል። 


 

በየአካባቢው በጎነትና ፍቅርን እንዳተረፉ የገለጸው ወጣቱ፣ በየክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መልማት ከቻለ ሀገርና ህዝብ መለወጥ እንደሚችል ግንዛቤ ማግኘታቸውንም ተናግሯል። 

ከሁሉም ክልሎች ተወጣጥተው እያከናወኑት ያለው የበጎፍቃድ አገልግሎት አብሮነት፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ግንኙነትን  ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳለው የገለጸችው ደግሞ ወጣት ሀና ተስፋዬ ናት።


 

በበጎፍቃድ አገልግሎቱ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በአንድነት እያከናወኗቸው ባሉ የልማት ሥራዎች ለነገ የኢትዮጵያ ከፍታ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጻ፣ በዚህም ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።

ወጣቶቹ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳና ሌሎች የልማት ሥራዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም