ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - የባሌ ዞን ነዋሪዎች

ባሌ ሮቤ ፤ ሐምሌ 13/2017 (ኢዜአ)፡-  ለታላቁ የኢትዮጵያ  ሕዳሴ ግድብ  ሲያደርጉት  የቆዩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የባሌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። 

የባሌ ሮቤ ከተማን ጨምሮ የዞኑ  የሕዝብ ተወካዮችና አመራሮች  ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ   ግድብ ዋንጫን ከምዕራብ አርሲ ዞን ዛሬ ተረክበዋል። 

ርክክብ የተካሄደው  የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በዲንሾ ከተማ ደማቅ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ ነው። 


 

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከታደሙት ነዋሪዎች መካከል አቶ ሐሰን አህመድ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያዊያን   የአንድነት  አርማ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ  ከፍጻሜ  ለማድረስ  በስጦታና በቦንድ ግዥ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 

አሁንም የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያና   የጋራ አሻራ የሆነው የሕዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያዊያንን የይቻላል መንፈስ ዳግም ያደሰው ለታላቁ የኢትዮጵያ  ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንደቀድሞ ሁሉ በቀጣይም  የሚጠበቅባቸውን እንደሚያበረክቱ  የገለጹት ደግም አቶ አበራ መንግሥቱ ናቸው።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኃይሌ፤ የዞኑ ነዋሪዎች  ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ውጤታማነት በቦንድ ግዥና በስጦታ በርካታ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።


 

አሁንም ግድቡ እስከሚመረቅ ድረስ   ሕብረተሰቡ፣ የፀጥታ አካላት እና ባለሃብቶች  ተሳትፏቸውን  እንዲያስቀጥሉ  የንቅናቄ ስራዎች እንደሚጠናከሩ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ላይ  ታላቁ የኢትዮጵያ  የሕዳሴ ግድብ በቅርቡ ለምረቃ እንደሚበቃ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም