አትሌት ሕይወት አምባው በአፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት ሕይወት አምባው በአፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/ 2017 (ኢዜአ)፦ በሶስተኛው የአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጨረሻ ቀን ውሎ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ ከቀትር በኋላ በተካሄደው ከ18 ዓመት በታች 5 ሺህ ሜትር ሴቶች ርምጃ ፍጻሜ አትሌት ሕይወት አምባው በማሸነፍ ለኢትዮጵያ በውድድሩ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች።
አትሌት ህይወት በሚገርም ብቃት እና ብቻዋን ውድድሩን በመምራት ማሸነፏን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የመጀመሪያውን ወርቅ ለማግኘት የውድድሩን የመጨረሻ ቀን ጠብቃለች። በውድድሩ ያገኘችውን የሜዳልያ ብዛት ወደ ስምንት ከፍ አድርጋለች።
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ተጨማሪ የፍጻሜ ውድድሮች ይደረጋሉ።
ከሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮና ዛሬ ማምሻውን ይጠናቀቃል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 30 ወንድ እና 27 ሴት አትሌቶች በድምሩ 57 አትሌቶችን አሳትፋለች።