ቀጥታ፡

የዳኝነትና የፍትሕ አገልግሎትን ማሻሻልና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የትኩረት ማዕከላችን ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2017(ኢዜአ)፦ የዳኝነትና የፍትሕ አገልግሎትን ማሻሻልና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የትኩረት ማዕከላችን ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍድር ቤት ምቹ የሥራ ከባቢን የፈጠረ ህንጻ እና የዲጂታል ልማት ፕሮጀክቶችን ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት እንዲሁም የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት በክልሉ የፍትሕ አገልግሎትን ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ ወደ ሪፎርም ገብቷል፡፡

በሪፎርሙ ለተቋም ግንባታና አደረጃጀት ማሻሻያ፣ ለሰው ኃይል ልማት እንዲሁም ውጤታማነትንና ቅልጥፍናን ለሚያሻሽሉ አሰራሮች ትኩረት በመስጠት ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በክልሉ የዳኝነት ስርዓት የህግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ በሚያስችል መልኩ ሪፎርም መደረጉን ገልጸው፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዲስ አመራር፣ የሰው ኃይል ግንባታ፣ የህግና አሰራር ማሻሻያ፣ የቴክኖሎጂ እንዲሁም ምቹ የሥራ ቦታ በመፍጠር ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

የላቀ የፍትሕ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን በመሰረታዊነት በመቀየር፣ የውሳኔዎችን ተገማችነትና የህዝብ እርካታን በሚያረጋግጥ መልኩ የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።


 

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውብና ጽዱ እንዲሁም ምቹ የስራ ከባቢ እና የችሎት ስርዓት ለማረጋገጥ ያልነበሩና አነስተኛ ችሎቶችን በማዘመን ቁጥራቸውንም በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን አስረድተዋል።

ለዳኝነት ስርዓት መሻሻል ተቋማዊ የትራንስፎርሜሽን ስራ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፥ በክልሉ ከመደበኛው የዳኝነት ጋር የሚተሳሰር የባህል ዳኝነት እውቅና የሚሰጥ ህግ መውጣቱንም ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት የልማትና የፍትሕን ጥብቅ ቁርኝት በመገንዘብ ገለልተኛና ጠንካራ የዳኝነት ተቋማት ግንባታን እውን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በቀጣይም የፍትሕና የርትዕ ጥያቄውን በመመለስ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ አበክረን እንሰራለን ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳነት አለም አንተ አግደው በበኩላቸው፥ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምቹ ባልሆነ የስራ ከባቢ አገልግሎቱን ሲሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡


 

በመሆኑም ምቹ የስራ ከባቢ ለመፍጠር የነባር ህንጻዎች እድሳት፣ የዳኝነት የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክቶችን በማከናወን ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

የዲጂታል ልማት ስራዎቹ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ችሎቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ስማርት ችሎትን በማስጀመር ውሳኔ አሰጣጥን ግልፅና ቀልጣፋ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና የወረዳ ፍርድ ቤቶች አሁንም ምቹ ባልሆነ የስራ ከባቢ እየሰሩ የሚገኙ በመሆናቸው በቀጣይ በትኩረት ለውጥ ለማምጣት የሁሉም ጥረት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም