ጀርመን ለግማሽ ፍጻሜ ደረሰች - ኢዜአ አማርኛ
ጀርመን ለግማሽ ፍጻሜ ደረሰች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2017(ኢዜአ)፦ በ14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ የመጨረሻ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ጀርመን ፈረንሳይን በመለያ ምት አሸንፋለች።
ማምሻውን በሴይንት ጃኮብ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ግሬስ ጌዮሮ በ15ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረችው ግብ ፈረንሳይን መሪ አድርጓል።
በ25ኛው ደቂቃ ስጆኬ ኑስከን ጀርመንን አቻ ያደረገችውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
የጀርመኗ ካትሪን ሄንድሪች በ13ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብታለች።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ በመጠናቀቁ ወደ ተጨማሪ ሰዓት ያመራ ሲሆን
በጭማሪ ሰዓትም ግብ አልተቆጠረም።
ወደ መለያ ምት ያመራው ጨዋታ በጀርመን የ6 ለ 5 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ፈረንሳይ የቁጥር ብልጫው ኳስ እንድትቆጣጠር እና ግልጽ የግብ እድሎች እንድትፈጥር ቢያደርጋትም ወደ ውጤት መቀየር አልቻለችም።
አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ10 ሰው የተጫወተችው ጀርመን ያሳየችው የአልሸነፍ ባይነት መንፈስ አድናቆት አስችሯታል።
ውጤቱን ተከትሎ የስምንት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ጀርመን ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች። ለፍጻሜ ለማለፍ ከስፔን ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ጣልያን ከእንግሊዝ ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ነው።
የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ሐምሌ 15 እና 16 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።