በክልሉ ቆይታ የሚያደርጉ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች አብሮነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ያተኩራሉ -ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ቆይታ የሚያደርጉ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች አብሮነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ያተኩራሉ -ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ሐምሌ 12/2017 (ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ቆይታ የሚያደርጉ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አብሮነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ እንደሚያተኩሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
’’በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ’’ 4ኛ ዙር የ2017 ዓ. ም የወሰን ተሻጋሪ በጎፈቃደኛ ወጣቶች ቡድን አባላት ዛሬ ማምሻውን ጋምቤላ ደርሰዋል።
ርዕሰ መስተዳድሯ ለወሰን ተሻጋሪ በጎፈቃደኛ ወጣቶች አቀባበል ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ሰላምን በማጽናት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከወጣቱ ኃይል የላቀ ድርሻ ይጠበቃል።
በተለይም እንደ ሀገር የተጀመረው የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎፈቃድ አገልግሎት ሰላምን ለማጽናት፣ በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር ረገድ የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የዘንድሮ የወሰን ተሻጋሪ በጎፈቃደኛ ወጣቶች ቡድን ያገኙትን እድል በመጠቀም በቆይታቸው ከልማት ስራዎች በተጨማሪ አብሮነትና አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ።
በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳደሯ ገልጸዋል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ በበኩላቸው ወሰን ተሻጋሪ የበጎፈቃድ አገልግሎት የህዝቡን የእርስ በእርስ ግንኙነትንና አብሮነትን እያጋመደ ያለ መርሀ ግብር ነው ብለዋል።
መርሃ ገብሩ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ገጽታና ፣በህዝቡ መካከል ያለውን ፍቅርና አንድነት እንዲረዳ ጭምር አበርክቶው የጎላ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።
ወሰን ተሻጋሪ የበጎፈቃድ ወጣቶች ቡድን በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ ከክልሉ ወጣቶች ጋር በመሆን፣ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ፣ በደም ልገሳ ፣ በአካባቢ ጽዳትና ሌሎች የበጎፈቃድ አገልግሎቶችን እንደሚያከናወኑ ይጠበቃል።