በአፍሪካ የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው አምስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው አምስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12 /2017(ኢዜአ):- በናይጄሪያ አቡካታ እየተካሄደ የሚገኘው ሶስተኛው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
በሻምፒዮናው የዛሬ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው አምስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ በርዝመት ዝላይ ሴት ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ኛቾክ ቾል የምትሳተፍ ሲሆን ወርቅነህ አይናለም በ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ምሽት 12 ሰዓት 15 ላይ ውድድሩን ያደርጋል።
በ5000 ሜትር ወንዶች ከ20 ዓመት በታች ፍጻሜ ምሽት 3 ሰዓት ከ20 ላይ ይካሄዳል። ንብረት ክንዴ እና ጌታሁን በላቸው ይሳተፋሉ።
የሴቶች የዱላ ቅብብል (Medley Relay) ከ18 ዓመት በታች ፍፃሜ ምሽት 3 ሰዓት ከ45 ላይ ይደረጋል።
ሰንቦኔ ተስፋ፣ገነት አየለ፣ ባንቻአለም ቢክስ እና ቦንቱ ዳኒኤል ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ5 ላይ በ4x100 ሜትር ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ሰላማዊት ኮከብ፣ ደሚቱ ሽፈራሁ፣ አጃይባ አሊዬ እና ትዕግስት ባንቲይደሩ ይወዳደራሉ።
ኢትዮጵያ እስከ አሁን በሻምፒዮናው ሶስት የብር እና አራት የነሐስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎችን ማግኘቷን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ሶስተኛው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል።