ቀጥታ፡

የከተማዋን እድገት የሚመጥን የፖሊስ ኃይል የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ኮሚሽነር ጌቱ አርጋዉ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 12/2017 (ኢዜአ):-የከተማዋን እድገት የሚመጥን የፖሊስ ኃይል የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋዉ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሌጅ ለ3ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ሞዴል ፖሊስ ስልጣኞች አስመርቋል።

በምረቃ መርሃ ግብር የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋዉ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ተከታይ ያዜ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋዉ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ፥ የመዲናዋ ሠላም ተጠብቆ እንዲቀጥል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል።

በወንጀል መከላከል፣ ምርመራና በትራፊክ ቁጥጥር ስራዎች እንዲሁም በሌሎች ፖሊሳዊ አገልግሎቶች የመፈጸም አቅም ማደጉንም ገልጸዋል።

የዛሬ ተመራቂዎችም ከተማዋ በሁሉም መስክ እያከናወነቻቸው ያሉ የልማት ስራዎች ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆኑ የሚሰጣቸው ተግባር ጠንክሮ መፈጸም እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በቀጣይም የከተማዋን እድገት የሚመጥን ፖሊስ ኃይል የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ተከታይ ያዜ በበኩላቸው፥ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ተልዕኮውን በሚገባ የመፈፀም ብቃት ለማሳደግ አጫጭርና መደበኛ ስልጠናዎችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፥የዛሬዎቹን ሞዴል ፖሊስ አባሎችን አሰልጥኖ ለምርቃ ማብቃቱን ተናግረዋል።

ተመራቂ ሞዴል ሰልጣኞች ጥብቅ የሆነውን የኮሌጁን ስልጠና ያለፉ እና የሚሰጣቸውን ግዳጅ በአግባቡ መወጣት የሚችሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ተመራቂ ኮንስታብል ኑርልኝ አቅናቸው፣ ኮንስታብል ተስፋነሽ ካሳ እና ምክትል ሳጅን ምትኩ ሀይለማርያም እንዳሉት፥ በኮሌጁ በነበራቸው ቆይታ ለሚሰጣቸው ግዳጅ ብቁ የሚያደርጋቸውን ስልጠና አግኝተዋል።

በቀጣይ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም