ኢትዮጵያ በ2ኛው የተመድ ሥርዓተ-ምግብ ጉባኤ በዘርፉ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች በተሞክሮነት ለዓለም ታካፍላለች - የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በ2ኛው የተመድ ሥርዓተ-ምግብ ጉባኤ በዘርፉ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች በተሞክሮነት ለዓለም ታካፍላለች - የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 12/2017 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ የምታስተናግደው 2ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ሥርዓተ-ምግብ ጉባኤ በሥርዓተ-ምግብ ሽግግር የተመዘገቡ ውጤቶችን በተግባር ለማሳየት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ እና ጣሊያን መንግስታት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመሆን ያዘጋጁት ሁለተኛው የተመድ የሥርዓተ-ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በአሜሪካ ኒዩርክ የሥርዓተ ምግብ ዕድሎችና ፈተናዎች እንዲሁም የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ በመምከር አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ቅድመ ጉባኤ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
በመቀጠልም እንድ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2021 በጣልያን ርዕሰ መዲና ሮም የመጀመሪያው የተመድ የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማረጋገጥ ባስመዘገበችው ተጨባጭ ውጤት 2ኛውን ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመርጣለች፡፡
ኢትዮጵያ የተመድ ሥርዓተ ምግብ ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ አንድምታው ትልቅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በጉባኤ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ የተለያዩ የአለም ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የምርምር ተቋማትና የዘርፉ ተዋንያን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል ።
ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል ሀገራት እንዴት መተባበር እንዳለባቸው ምክክር እንደሚደረግበት ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በሥርዓተ ምግብ ላይ የሚያደርሱት ጫና በዝርዝር እንደሚታይ ገልጸው፤ ሀገራት ተባብረው ዜጎች ጤናማ ምግብ ማግኘት የሚችሉበትን የጋራ መፍትሔ ሀሳብ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም እንዲሁ፡፡
በዚህም ጉባኤው ኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግርን እውን ለማድረግ ያከናወነቻቸውን ዋና ዋና ተግባራት ለዓለም የምታቀርብበት የሌሎችን ተሞክሮ የምትቀስምበት መድረክ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ለማፋጠን ወደ ትግበራ በመግባት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡
መንግስት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለፋይናንስና የሰው ሃይል ልማት መሟላት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ከእርሻ ጀምሮ እስከ ምግብነት ያለውን የእሴት ሰንሰለት በማስተባበር የተገኘ ውጤት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሮች ጨምሮ በሌሎች ኢንሼቲቮች የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳለጥ ተስፋ ሰጭና የሚታይ ስኬት ማስመዝገብ መቻሏንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሥርዓተ-ምግብ ሽግግር የሚመራበት መንገድ የተለየ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም ጉባኤውን ለማስተናገድ እንድትመረጥ አስችሏታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሥርዓተ-ምግብ ሽግግር ዋና አስተባባሪና የግብርና ሚኒስትሩ ዋና አማካሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ስንዴ ከውጭ ታስገባ የነበረበትን ዘመን አስታውሰዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ታሪክ በመቀየር የራሷን ፍጆታ በመሸፈን ወደስንዴ ላኪነት መሸጋገሯን ተናግረዋል።
በዚህም ያስመዘገበችውን ልምዷንና ስኬቷን ለዓለም ማቅረብ እንድትችል ጉባኤውን እንድታስተናግድ ተመርጣለች ብለዋል፡፡
ዶክተር ጌታቸው እንደገለጹት ሶስት ቀናት በሚካሄደው የተመድ የሥርዓተ ምግብ ጉባኤ ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሰራቻቸውን ውጤታማ ሥራዎች በጉባኤው ተሳታፊዎች ይጎበኛሉ፡፡