ቀጥታ፡

ጨፌው ባደረገው ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል

አዳማ፤ሐምሌ 12/2017(ኢዜአ)፦ጨፌው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባደረገው ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር የህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለፁ ።

የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 4ኛ ዓመት ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ ገልማ ጨፌ መካሄድ ጀምሯል።


 

አፈጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የህዝቡ ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነትና የአገልግሎት እርካታ መረጋገጥ እንዲችል ጨፌው ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር አድርጓል።

ወጣቶችና ሴቶች የልማት ኃይል እንዲሆኑና ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ እንዲጠናከር ከማስቻል አኳያ የተሻለ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም ፈተናዎችን በመቋቋም በክልሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዘርፎች በታቀደላቸው ጊዜ አመርቂ ስራዎች መከናወን እንደቻሉም አስረድተዋል።

የክልሉ መንግሥት ሰላምና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በተሻለ ደረጃ የፈፀመበት ዓመት እንደሆነ አውስተው፥በተለይ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን በመቅረጽ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወነው ስራ ውጤት የተገኘበት መሆኑንም አመልክተዋል።


 

በተያዘው ክረምት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአቅመ ደካማ ቤቶችና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች የማከናወን ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ጨፌው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የልማት ዕቅድ ክንውንና የ2018 ዓ.ም የመነሻ ዕቅዶችና በጀት ላይ በጥልቀት በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም አክለዋል።

አፈጉባኤዋ እንዳመለከቱት፤ ጨፌው በቆይታው የክልሉ መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የልማት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የክልሉ ኦዲት መስሪያ ቤት የስራ ክንውን፣ የ2018 በጀትን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመወያየት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም