የ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ማንሰራራት በሚያጸና መልኩ ለማሳካት የአመራሩ ትጋትና የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ማንሰራራት በሚያጸና መልኩ ለማሳካት የአመራሩ ትጋትና የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ):-የ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ማንሰራራት በሚያጸና መልኩ ለማሳካት የአመራሩ ትጋትና የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ።
የመንግሥት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት አቅድ የግምገማ መድረክ በፌደራል ተቋማት አመራሮች ደረጃ ተካሂዷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት፥ በ2017 በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች የላቀ ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ፣ በማዕድን እና በቡና ወጪ ንግድ፣ በተኪ ምርት እና በሌሎች ዘርፎች በታሪክ ከፍተኛ ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅም የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
የተመዘገቡ ስኬቶች በቅንጅት የመጡ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ሀገርና ህዝብን የሚያኮሩ እና ለአዳዲስ ድል እንድንነሳ ስንቅ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ አመራሮች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ አስደናቂ እመርታዎች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅም በራስ አቅም ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ ምሳሌ፣ የጀግንነትና የወል ትርክት አምድ፣ የኢትዮጵያውያን የይቻላል ትጋት ማሳያ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን ተከትሎ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በአምራች ኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ልህቀት ወሳኝ ስኬቶች መጥተዋል ነው ያሉት።
መንግሥት ጥራት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስቀጠል ለአምራች ዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦትን ማጠናከሩንም አውስተዋል።
በቀጣይም ሙስናን የመከላከል፣ ዘላቂ ሰላምን የማጠናከር አገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ለውጥ ቢመጣም በፌደራልና በክልሎች መካከል የተናበበ አሰራርና አፈጻጸም ባለመኖሩ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፥ የዘንድሮው ሀገራዊ እቅድ የ2017 በጀት ዓመት ስኬቶችን፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ተሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ጥራት ያለው ስኬት ለማስመዝገብ መታቀዱንም ጠቁመዋል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግም የፌደራል ተቋማትና ክልሎች ወጥ የሆነ አሰራርን እንዲተገብሩና የተሳለጠ ምህዳር እንዲፈጥሩ ይደረጋል ነው ያሉት።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ በሰጡት ማጠቃለያ፥ መንግሥት የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ በልማት እያጸና እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለዚህም በ2018 በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ አዳዲስ እመርታዎችን ለማስመዝገብ ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ገብቷል ነው ያሉት።
ሀገራዊ ዕቅዱ ታላላቅ ስኬቶችን ያለመ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በከፍታ ለማስቀጠል የአመራሩ የሌት ተቀን ትጋት ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
በእቅዱ ላይ መግባባት ፈጥሮ በአርዓያነት መስራት፣ የመንግሥት ሰራተኛውን፣ የግሉን ዘርፍ እና የህዝቡን ተሳትፎ በጉልህ በማሳደግ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እና ለወል ትርክት መጠናከር ሁሉም መስራት አለበት ነው ያሉት።