የመጅሊስ አመራሮችን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ህዝበ ሙስሊሙ እድሉን ሊጠቀም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የመጅሊስ አመራሮችን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ህዝበ ሙስሊሙ እድሉን ሊጠቀም ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ)፡- ህዝበ ሙስሊሙ የመጅሊስ አመራሮችን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በመውሰድ መሪዎቹን የመወሰን እድሉን እንዲጠቀም የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።
የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ኡስታዝ በድሩ ኑሩ፤ የመጅሊስ ምርጫን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ኡስታዝ በድሩ ኑሩ፤ በመግለጫቸው ቦርዱ ምርጫውን የተሳካ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በሂደቱን አሁን ላይ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ህዝበ ሙስሊሙ የመጅሊስ አመራሮችን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የመወሰን እድሉን እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።
እጩ የመለየትና ጥቆማ የመስጠቱ ሂደት ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 4 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን የኡለማዎች ምርጫ ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል ብለዋል።
በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ በንቃት በመሳተፍ ሊመሩ የሚችሉ በቂ ልምድና እውቀት ያላቸውን አመራሮች እንዲመርጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምክር ቤቱ የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ፀሐፊ መሃዲ ሸምሱ፤ በክልሉ የመጅሊስ ምርጫ ምዝገባ ከተጀመረ ወዲህ በርካቶች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን አስታውሰው በቀሩት ጥቂት ቀናት ሌሎችም ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም እድሜው 18 ዓመት የሞላው ሙስሊም መመዝገብ እንደሚችል ተመልክቷል።