የአካል ጉዳተኞችን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ተዘጋጅቷል

አዳማ ፤ ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ):-በኢትዮጵያ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አካታች ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ የፖሊሲ ሠነድ መዘጋጀቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲ ሠነድ ዝግጅት ግብዓት ለማሰባሰብ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሄዷል።

በወቅቱም የሚኒስቴሩ የህግ አማካሪ አቶ ደረጄ ተግበሉ እንደገለፁት፤ የአካል ጉዳተኞችን መሰረታዊ መብቶች በማስከበርና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ ክፍተቶች ይስተዋላሉ።

በመሆኑም የፖሊሲ ዝግጅት ማድረግ ማስፈለጉንና ዋና ዓላማውም የአካል ጉዳተኞችን የእኩል እድል ተጠቃሚነትና ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ የፖሊሲ እርምጃዎችን ለመውሰድ መሆኑንም አመልክተዋል።

ይህም ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዱ አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልፀው ለ5ኛ ጊዜ የግብዓት ማሰባሰብ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሄዷል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማህበራዊ ልማት፣ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) መንግስት አካል ጉዳተኞች የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው ሀገሪቱ እስካሁን የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ፖሊሲ ስለሌላት የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር ሳይቻል መቆየቱን አስታውሰዋል።

መንግስት የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲ ለማውጣት ቁርጠኛ አቋም መያዙን አድንቀው ፖሊሲው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝም አመልክተዋል።


 

በመድረኩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ እንዲሁም የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም