በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚዘጋጁ ኤግዚቢሽን እና ባዛሮች የአምራች እና የሸማቹን የገበያ ትስስር እያጠናከሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚዘጋጁ ኤግዚቢሽን እና ባዛሮች የአምራች እና የሸማቹን የገበያ ትስስር እያጠናከሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ):-በከተማ አስተዳደሩ የሚዘጋጁ ኤግዚቢሽን እና ባዛር የአምራች እና የሸማቹን የገበያ ትስስር እያጠናከሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሃቢባ ሲራጅ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ያዘጋጀውና ከሃምሌ 7 እስከ ሃምሌ 11/2017 ዓ/ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛር በዛሬው እለት ተጠናቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሃቢባ ሲራጅ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ቢሮው የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ከዚህ ውስጥ የንግድ ስርአቱን ቀልጣፋ እንዲሆን አምራች እና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት በኩል ውጤታማ ስራ መሰራቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡
2ኛው ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛርም የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ለ5 ቀናት በቆየው ኤግዚቢሽን እና ባዛር የአገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለህብረተሰቡ ትልቅ ፋይዳ ማስገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
በኤግዚቢሽን እና ባዛሩ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት መፈጸማቸውን አንስተው ከ43 ሚሊየን ብር በላይ ግብይት መከናወኑንም አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍስሃ ጥበቡ በበኩላቸው፤ ባዛሩ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የገበያ ትስስር የተፈጠረበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ቢሮው አቅራቢዎችና ሸማቾች በቀጥታ የሚገበያዩበት ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
ከሸማቾች መካከል አልማዝ አበበ እንደገለጸችው ከባዛሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን በመግዛት ተጠቃሚ መሆኗን ተናግራለች፡፡
ምርታቸውን በባዛሩ ያቀረቡት አቶ ደረጀ ጋሪ በበኩላቸው፤ ባዛሩ መዘጋጀቱ ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡