መገናኛ ብዙሃን የጋራ ትርክትን ለማስረጽ የጀመሩትን ውጤታማ ተግባራት አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

 

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ):-መገናኛ ብዙሃን የጋራ ትርክትን ለማስረጽ የጀመሩትን ውጤታማ ተግባራትን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2018 በጀት አመት እቅድ ላይ ከተቋሙ ባለሞያዎች ጋር ውይይት ተደርጎበታል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ኢዜአ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሀገራዊ አጀንዳዎችና ለሪፎርም ስራዎች ስኬት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና እያደረገች ላለችው ስኬታማ ጉዞ መሳለጥ፣ የህብረ-ብሔራዊ አንድነትና ወንድማማችነት ትርክትን ብሎም የሀገረ መንግስት ግንባታን ከማስረጽ አኳያ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በማተኮርም በኢኮኖሚ፣ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ዲፕሎማሲና ዘላቂ የሰላም ግንባታ ላይ የተለያዩ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ በርካታ ስራዎችን መስራቱን ተናግረዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን መንግስት ትኩረት ያደረገባቸውን ትላልቅ ጉዳዮች ማጉላት እንዳለባቸው ጠቁመው፤የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚመረቁበት ዓመት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሀገራዊ ምርጫ፣ወሳኝ የሰላም ጉዳዮች፣ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ዕድገት የሚጠበቅበት ብሎም ሌሎችም ተግባራት የሚከናወኑበት በጀት አመት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን የምታረጋግጥበት ዓመት መሆኑን የገለጹት ዶክተር ቢቂላ፤ መገናኛ ብዙሃንም እነዚህን አጀንዳዎች ጨምሮ ሌሎችንም ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስራ አመራር ቦርድ አባል ሚሊዮን ተረፈ በበኩላቸው፥ ኢዜአ በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ጉዳዮችን ወደ ህዝብ በማስረጽ ረገድ እምርታ ያላቸው ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።


 

ተቋሙ ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ሀገራዊ ተልእኮውን ይበልጥ በብቃት ለመወጣት መስራት እንዳለበትም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ የሪፎርም ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር የተሰጠውን አገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች፣ቀጣናዊና አካባቢያዊ ጉዳዮችና ሀገራዊ ምክክር ጨምሮ ሌሎች አጀንዳዎችን ለማስረጽ በእቅድ ከያዛቸው ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ፣የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣መልካም አስተዳደርና አገልግሎት፣ዲፕሎማሲና ሌሎች ሀገራዊ አጀንዳዎችን በዲጂታል አማራጮችና የተለያዩ የይዘት ስራዎችን በጥናት ላይ ተመስርቶ በጥልቀት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በዲጂታል አማራጮች በተለያዩ ቋንቋዎች የገጽታ ግንባታ ስራዎችን መሥራት ከዋነኛ የትኩረት መስኮች መካከል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም