በክልሉ መስህቦችን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ መስህቦችን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

ባሕርዳር፤ ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ):- በአማራ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መስህቦችን ከጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የስራ ክንውን የግምገማ መድረክ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ12 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና ከ27 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ክልሉን ጎብኝተዋል።
ባለድርሻ አካላትን፣ የቢሮውን መዋቅር ከላይ እስከታች በማቀናጀትና መገናኛ ብዙሃንን በአግባቡ በመጠቀም በተከናወነው የማስተዋወቅ ስራ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቀት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።በተለይም የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የቱሪዝም ፍሰቱ ከታቀደው በላይ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል የታየበት እንደሆነም አመልክተዋል።
የክልሉን ዕምቅ የባህልና የቱሪዝም አቅም በማስተዋወቅና መዳረሻዎችን በማልማት የተከናወነው ስራ ጨምሮ በበጀት ዓመቱ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት እንደተቻለ አስታውቀዋል።
የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች ፤ በባህል ልማትና እሴት ግንባታ በኩልም ሰፊ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበሩ የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ የእንግጫ ተከላና የቡሄ በዓላትን የቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ስራ በስፋት መከናወኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።