በትምህርት ዘርፍ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ዘርፍ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 11/2017(ኢዜአ)፦ከለውጡ ወዲህ በትምህርት ዘርፍ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ 150 የትምህርት ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት፤ በሁለንተናዊ ዘርፍ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ በአዕምሮና በአካል የዳበረ ትውልድ መገንባት ይገባል ብለዋል።
ይህን ከማረጋገጥ አኳያ ጥራት ያለው ትምህርት አይነተኛ ሚና እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት የለውጥ አመታት በትምህርት ዘርፍ ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገብ መቻሉንም አመላክተዋል፡፡
በመዲናዋ ከለውጡ ወዲህ 110 የሚሆኑ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተገነቡ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
30 ሺህ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ 334 የትምህርት ቤት የምገባ ማዕከላትና ሌሎች የትምህርት መሰረተ ልማቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት አመትም 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ 150 የትምህርት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል 14 የሚሆኑት አዳዲስ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በእርጅና ለመማር ማስተማር ምቹ ያልነበሩና የማስፋፊያ ግንባታ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሁለንተናዊ ብልጽግናን ያለትውልድ ግንባታ ማሰብ አይቻልም ያሉት ከንቲባዋ፤ በዚህም ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በተሰጠው ትኩረት የተማሪዎች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አመላክተው፤ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ትምህርት የአገራት እድገት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በዚህ መነሻነት ከተማ አስተዳደሩ ያከናወናቸው የትምህርት ማሻሻያ ርምጃዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነት ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክቱ ነው የገለጹት።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።