ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ባገኘነው ነጻ የህግ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነናል- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ባገኘነው ነጻ የህግ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነናል- ነዋሪዎች
አምቦ፤ ሐምሌ 11/ 2017 (ኢዜአ)፦- የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው ነጻ የህግ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን የአምቦ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲው በሰጠው ነጻ የህግ ድጋፍ 40 ሺህ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ መደረጋቸውም ተገልጿል።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ባቋቋመው ነጻ የህግ ድጋፍ ማዕከል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ገነት በቀለ እንዳሉት፤ የቤተሰቦቻቸውን የውርስ መሬት ካርታ ወጥቶበት አላግባብ እንደተወሰደባቸው አስታውሰዋል ፡፡
ጉዳዩን ወደ ህግ ወስደው ጠበቃ ቀጥረው ለመከራከር አቅማቸው ስላልፈቀደ ዩኒቨርሲቲው ባመቻቸላቸው የህግ ድጋፍ ተጠቅመው ያለ አግባብ የወጣው ካርታ እንዲመክን ተደርጎ ከውርስ መሬቱ ተጠቃሚ ለመሆን መቻላቸውን ገልፀዋል።
ከዩኒቨርሲቲው የህግ ድጋፍ ባያገኙ ኖሮ በህግ አግባብ ተከራክረው ከውርስ መሬቱ ተጠቃሚ ለመሆን አዳጋች ይሆንባቸው እንደነበርም አስረድተዋል።
ሌላኛዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ብዙነሽ ያደታ የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ ባለቤታቸው ሲሞት የራሳቸው የነበረውን መኖሪያ ቤት የባለቤታቸው ወንድም መኖሪያ ቤቱ ይገባኛል በማለት እንደተከራከራቸው ይናገራሉ፡፡
የንብረት ይገባኛል ክርክር በሚያደርጉበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው የህግ ማዕከል በከፈተው ነጻ የህግ አገልግሎት እገዛ ፍትህ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
“ይህ ድጋፍ ባይደረግልኝ ኖሮ እኔ ፍርድ ቤት ተመላልሼም ሆነ ቆሜ የምከራከርበት አቅም ስለሌለኝ ልጆቼን የማሳድግበት የራሴ ንብረት ይቀር ነበር” ብለዋል።
''በሃሰተኛ ምስክሮች አማካኝነት ተወስዶ የነበረን የእናቴን ንብረት ማዕከሉ ባደረገላት ነጻ የህግ ድጋፍ ፍትህ አግኝታለች'' ያለው ደግሞ የአምቦ ከተማ ነዋሪው ወጣት ምልኬሳ ጅፋራ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ከእናቱ በተጨማሪ በርካታ አቅመ ደካማ ወገኖች ፍትህ ማግኘታቸውንም ምስክርነት ሰጥቷል፡፡
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህርና የዩኒቨርሲቲው ነጻ የህግ አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ሞሲሳ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ ሰባት ማእከላት አማካኝነት ማዕከሉ 40 ሺህ ለሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የህግ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
አገልግሎቱን ካገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች መካከል፣ በህመም ላይ የሚገኙ፣ አካል ጉዳተኞች፣ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡
የህብረተሰብ ክፍሎቹ ካገኙት የሕግ አገልግሎት መካከልም የህግ ምክር፣ ጥብቅና የመቆም፣ ክስ የመመስረት፣ የተለያዩ ሰነዶችንና ማመልከቻዎችን የማዘጋጀት የመሳሰሉት መሆናቸውን አብራርተዋል።
ማዕከሉ የሰጠው ነፃ የህግ ድጋፍ ተጠቃሚ ነዋሪዎቹ ያወጡት የነበረን ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማስቀረቱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።