በሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ):- በሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ተሰጥቷል።    

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በአገራዊ ምክክር ሂደቱ  ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ለማሳተፍ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል።     

ለዚህም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎች ጋር በሕግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎች በምክክር ሂደቱ ተሳታፊ መሆን በሚችሉበት ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።      

በውይይቱም በህግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎችን ማሳተፍ ገንቢ ሚና እንዳለው የጋራ መግባባት  ላይ መደረሱንም  ተናግረዋል። 

በቀጣይም በፌዴራል እና በክልል ማረሚያ ቤት ያሉ ዜጎችን ተሳታፊ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።           

በሌላ በኩል በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አቶ ጥበቡ በመግለጫቸው  አብራርተዋል።      

በዚህም በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኞቹ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።      

እናት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፓርቲዎች ቅደመ ሁኔታ በማስቀመጥ በምክክር ሂደቱ ከመሳተፍ መታቀባቸውን ተከትሎ ኮሚሽኑ ውይይት ማድረጉን ጠቅሰው፤  በዚህም ገንቢ ሀሳቦች ተነስተዋል ብለዋል።     

በምክክሩ ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳተፉ የቆዩ ፓርቲዎችን ወደ ምክክሩ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።       

ኮሚሽኑ በምክክሩ የሴቶች ተሳትፎን ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንንም ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አባላት ጋር ባደረገው ውይይት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን እንዲወጡ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም