የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባዔ ነገ በአዳማ ከተማ ይካሄዳል

አዳማ፤ ሐምሌ 11/2017(ኢዜአ)፦ የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን፣ 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባዔ ነገ በአዳማ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለፀ።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመላከቱት በጉባኤው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ።

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የክልሉ መንግስት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የጨፌው ፅህፈት ቤት ሥራ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደሚፀድቅ አፈ ጉባዔዋ ገልጸዋል።

በጉባኤው የሰላም እና የፀጥታ ጉዳይ፣ የልማት ሥራዎች ክንውን፣ የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ዋነኛ የትኩረት ጉዳዮች መሆናቸውንም አፈጉባዔዋ አስታውቀዋል።

እንዲሁም የኦዲት ግኝት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የዓመቱ እቅድና አፈጻጸም ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት አስታውቀዋል።

የጨፌው ቋሚ ኮሚቴዎች የድጋፍና ክትትል አፈጻጸም ሪፖርትም ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል።

በተጨማሪም ጉባዔው በሁለት ቀናት ውሎው የ2018 የክልሉ በጀት እና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ወይዘሮ ሰአዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም