የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማውረስ ለሚደረገው ጥረት የላቀ አበርክቶ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማውረስ ለሚደረገው ጥረት የላቀ አበርክቶ አለው

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 11/2017(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማውረስ ለሚደረገው ጥረት የላቀ አበርክቶ እንዳለው ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጋምቤላ ሪጅን የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ‹‹በመትከል ማንሰራራት›› በሚል መሪ ሃሳብ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሂደዋል፡፡
የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሳይመን ሙን(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት እተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገርን ለማውረስ ለሚደረገው ጥረት የላቀ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሀገር የተያዘውን ግብ ማሳካት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጋምቤላ ሪጅን የሥራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በማከናወን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብለዋል፡፡
ሌሎች ተቋማትም ይህንኑ አርዓያ በመከተል በክረምቱ ወራት በሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ላይ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡
የጋምቤላ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳይሬክተር አማረ ገብረመድህን በወቅቱ እንዳሉት የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የሁሉንም ተቋማት የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡
አገልግሎቱ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት እንደሀገር በተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ላይ በትኩረት ሲሳተፍ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማትም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር የተራቆቱና የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ችግኞችን እየተከሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ችግኝ መትከል ብቻ ግብ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ ዛሬ የተተከሉትን ችግኞች ከእንስሳት ንክኪ የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱም ተናግረዋል፡፡
ከሪጅኑ ሰራተኞች መካከል አቶ ይርጋለም ገነቴ እና አቶ አበበ ለማ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ችግኝ በመትከል አሻራችንን በማሳረፋችን ተደስተናል ብለዋል፡፡
ዛሬ የተከሏቸውን ችግኞች ተንከባክበው ለጽድቀት እንደሚያበቁ ጠቅሰው በቀጣዮቹ የክረምቱ ወራት የጀመሩትን የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡