የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ):- በ13ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሁለት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ናይጄሪያ ከዛምቢያ ምሽት 1 ሰዓት ላይ በላርቢ ዛውሊ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የዘጠኝ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ በምድብ ሁለት በሰባት ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዛ ሩብ ፍጻሜ ገብታለች።
ተጋጣሚዋ ዛምቢያ በምድብ ሁለት በሰባት ነጥብ ሁለተኛ በመሆን ስምንት ውስጥ ገብታለች።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
እ.አ.አ በ2022 በሞሮኮ በተካሄደው 12ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ለመያዝ ባደረጉት ጨዋታ ዛምቢያ ናይጄሪያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ጋና እ.አ.አ በ2018 ባዘጋጀችው 11ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ናይጄሪያ ዛምቢያን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ረታለች።
በናሚቢያ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2014 በተካሄደው 9ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ናይጄሪያ 6 ለ 0 ማሸነፍ ችላለች።
በሶስቱ ጨዋታዎች ናይጄሪያ 11 ግቦችን ስታስቆጥር ዛምቢያ ከመረብ ላይ ያሳረፈችው 1 ጎል ብቻ ነው።
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ተመጣጣኝ ፉክክር ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ናይጄሪያ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች።
የጨዋታው አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
ምሽት 4 ሰዓት ላይ በፕሪስን ሙላይ አብደላ ስታዲየም የሚካሄደው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አዘጋጇ ሞሮኮ እና ማሊን ያገናኛል።
ሞሮኮ በምድብ በሰባት ነጥብ አንደኛ ደረጃን በመያዝ፣ ማሊ በምድብ ሶስት በአራት ነጥብ ምርጥ ሶስተኛ በመሆን ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በውድድር እና የወዳጅነት ጨዋታዎች ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ተገናኝተው በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሞሮኮ 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ ማሊ 9 ጎሎችን አስቆጥራለች።
በዛሬው ጨዋታ ሞሮኮ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንደምትወስድ የሚጠበቅ ሲሆን ማሊ የመልሶ ማጥቃት እና የፈጣን ሽግግር እንቅስቃሴ ይዛ ወደ ሜዳ ትገባላች ተብሎ ይጠበቃል። ሞሮኮ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች።
የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከአልጄሪያ እና ጋና አሸናፊ ጋር ይገናኛል።