ስፔን እና ስዊዘርላንድ በሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት ይፋለማሉ - ኢዜአ አማርኛ
ስፔን እና ስዊዘርላንድ በሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት ይፋለማሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2017(ኢዜአ):- 14ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ሶስተኛ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ዛሬ በስፔን እና ስዊዘርላንድ መካከል ይካሄዳል።
ጨዋታው በዋንክዶርፍ ስታዲየም ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
ስፔን በምድብ ሁለት ዘጠኝ ነጥብ በማግኘት የምድቧ መሪ ሆና ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
በምድብ አንድ የነበረችው የውድድሩ አዘጋጅ ስዊዘርላንድ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ስምንት ውስጥ ገብታለች።
ሁለቱ ቡድኖች እስከ አሁን ስድስት ጊዜ ተገናኝተው ስፔን አምስት ጊዜ ስታሸንፍ ስዊዘርላንድ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷታል።
ስፔን በጨዋታዎቹ 25 ግቦችን ስታስቆጥር ስዊዘርላንድ 8 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
እ.አ.አ በ2023 በአውሮፓ የሴቶች የኔሽንስ ሊግ ውድድር ስፔን ስዊዘርላንድን 7 ለ 1 ያሸነፈችበት ጨዋታ በሀገራቱ የእርስ በእርስ ግንኙነት ከፍተኛ የግብ መጠን የተቆጠረበት ሆኖ ተመዝግቧል።
ስፔን ስዊዘርላንድን ባሸነፈችባቸው ጨዋታዎች በአማካይ አራት ግቦችን አስቆጥራለች።
ሁለቱ ሀገራት ያላቸው የእርስ በእርስ ግንኙነት ስፔን ከፍተኛውን ብልጫ ትወስዳለች።
በውድድሩ ላይ አራተኛ ተሳትፎዋን እያደረገች የምትገኘው ስፔን ትልቁ ውጤቷ እ.አ.አ በ2022 እንግሊዝ ባሰናዳችው 13ኛው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የደረሰችበት ነው።
በአንጻሩ ለሶስተኛ ጊዜ እየተሳተፈች ያለው ስዊዘርላንድ ከምድቡ ስታልፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዛሬው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ስፔን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች።
የጨዋታው አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከፈረንሳይ እና ጀርመን አሸናፊ ጋር ይጫወታል።