በኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ስልጠናውን እየወሰዱ ይገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2017(ኢዜአ) በኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠናን ሐምሌ 2016 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወሳል።

ስልጠናው በዋናነት በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ ስዩም መንገሻ ለኢዜአ እንደገለጹት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወሳኝ ከሆኑ መሰረቶች አንዱ የዲጂታል ስነ-ምህዳሩን ማስፋት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የዲጂታል ስነ ምህዳሩን ከሚያሰፉ ስራዎች መካከልም ዋነኛው የክህሎት ግንባታ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ እውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ሀይል ማፍራት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኮደርስ ስልጠናው የዜጎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማዳበር እንደሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በዚህም እስካሁን ባለው የስልጠናው ሂደት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የኮደርስ ስልጠናን እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን በኢኒሼቲቩ በተሰራው ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስልጠናውን ካጠናቀቁ ወጣቶች መካከል 900ሺህ የሚሆኑት የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና ሀገራዊ ተግባር መሆኑን ገልጸው፤ ክልሎችም የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በዚህም የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ መኖራቸውን ነው ስዩም መንገሻ ጨምረው የገለጹት።

የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ወጣቶች በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ንቁ ተሳታፊ እና አምራች እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ክህሎት የሚያገኙበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በተያዘው ክረምት ወቅትም ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስልጠናውን በመውሰድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም