የብሩንዲው ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ የሳሄል ቀጣና ልዩ ልዑክ ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር እና የአንጎላ ፕሬዝዳንት ጆኣኦ ሎሬንቾ የብሩንዲውን ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬን የሳሄል ቀጣና ልዩ ልዑክ ሆነው እንዲያገለግሉ መርጠዋቸዋል። 

ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ህብረት የወጣቶች፣ ሰላም እና ደህንነት አጀንዳ ልዩ አስተባባሪም ናቸው። 

ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የሳሄል ቀጣና የደህንነትና ሰብዓዊ ፈተናዎች የመፍታት የፖለቲካ ተልዕኮን መቀበላቸውን የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል።

ልዩ ልዑክ ሆነው የተመረጡት ፕሬዝዳንቱ ህብረቱ በሳሄል ቀጣና ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ በአዲስ መልክ የጀመራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ይመራሉ።

በተሰጣቸው ኃላፊነት ከመንግስታት፣ ቀጣናዊ ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ውይይቶች እንዲደረጉ፣ መግባባት እንዲፈጠርና ዘላቂ ሰላምና ደህንነት የሚያመጡ ስትራቴጂዎችን የመደገፍ እና የመተግበር ስራዎችን ያከናውናሉ።

የልዩ ልዑኩ ሚና ውስብስቡን የሳሄል ቀጣና ቀውሶች ሁሉን በማሳተፍ እና የተቀናጀ ምላሽ በመስጠት ለመፍታት ያለውን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ተመላክቷል።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ጆኣኦ ሎሬንቾ የብሩንዲው ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ የካበተ የፖለቲካ ልምድ ያላቸውና ጠንካራ የፓንአፍሪካ ተሟጋች እንደሆኑ ገልጸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እንደሚወጡ ሙሉ እምነቴ ነው ብለዋል።

የልዩ ልዑኩ ሹመት የአፍሪካ ህብረት ለቀጣናዊ ትስስር፣ ለሰላም ግንባታና በአፍሪካ የተኩስ ድምጽ እንዳይሰማ የማድረግ ትልቅ ራዕይ እንዲሳካ ያለውን ጽኑ አቋም እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

ሊቀ መንበሩ ሁሉም የአፍሪካ ህብረት አደረጃጀቶች፣ አባል ሀገራት እና የልማት አጋሮች የልዩ ልዑኩን የሳሄል ቀጣና ስራ እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም