የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን የፖለቲካ ተሳትፎ ያሳድጋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2017(ኢዜአ)፦ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን የፖለቲካ ተሳትፎ እንደሚያሳድግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ዛሬ ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው ማሻሻያ የተደረገበትን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን አፅድቋል።

በዚሁ አዋጅ 26 አንቀፆች እንደተሻሻሉ የተገለጸ ሲሆን፥ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፥ የአዋጁን የማሻሻያ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

በዚሁ ጊዜ አዋጁ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊና ግልፅ በሆነ መልኩ ማካሄድ እንዲያስችል መሻሻሉን አንስተዋል።

ማሻሻያ ከተደረገባቸው አንቀፆች መካከል የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች የምርጫ ተሳትፎ፣ የቅሬታ አቀራረብ፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች የፋይናንስ ምንጭና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ይገኙበታል ብለዋል።


 

የምክር ቤቱ አባላትም የማሻሻያ አዋጁ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን የፖለቲካ ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ የምርጫ ስራውን በቴክኖሎጂ ለማገዝ እንደሚያስችል አንስተዋል።

ይሁንና በማሻሻያ አዋጁ ላይ በምርጫ ጣቢያዎች የነበረው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እንዲቀር መደረጉ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ተነስቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እውነቱ አለነ በሰጡት ምላሽም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባሉት ከ50ሺህ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችን ማቋቋም አስፈላጊነቱ እምብዛም መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም ቅሬታ ከምርጫ ክልል ጀምሮ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የሚቀርቡበት አማራጭ አዋጭ መሆኑ እንደታመነበት አስረድተዋል።


 

በሌላ በኩል የማሻሻያ አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረትን በተመለከተ ማሻሻያ ለምን እንዳልተደረገበትም የምክር ቤቱ አባላት አስንተዋል።

የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ በሰጡት ምላሽም የፖለቲካ ፓርቲዎች በፈለጉት መንገድ የመደራጀት መብት ሕገ-መንግስታዊ መሆኑን አብራርተዋል።

የተሻሻለው አዋጅ የምርጫ ሥራን በተሻለ መልኩ መምራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን በመግለጽ።

ውስብስብ የሆነውን የምርጫ ሂደት በቴክኖሎጂ በማገዝ ግልፅ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ምርጫ ማካሄድ እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ አዋጅን በሁለት ተቃውሞ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም