የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት የገበያ ድርሻ ወደ 41 በመቶ አድጓል-የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 10/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት ለሀገር ውስጥ የመድሃኒት አምራቾች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት የገበያ ድርሻ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ገለጹ።

የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የካሳቫ ስታርች ምርት የአዋጭነት ጥናትን ለፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ለባለድርሻ አካላት ይፋ አድርጓል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በዚሁ ወቅት ፥ የሀገር ውስጥ የመድሀኒት ማማረት አቅምን ለማሳደግ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውንና አርማወር ሀንሰን ኢንስቲትዩት በጥናትና ምርምር በመደገፍ  ውጤት ማስገኘቱን አንስተዋል።

መንግስት የጤና ስርዓቱን ፍትሀዊነት እና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የፖሊሲ ክለሳ ማድረጉን በማውሳት፥ ለሀገር ውስጥ የመድሃኒት አምራቾችም ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጀምሮ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

በመድሃኒት ግዥ ሂደትም የሀገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች የሚያቀርቧቸው መድሃኒቶች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት መጨመሩን እና የገበያ ድርሻውም ከ8 በመቶ ወደ 41 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከግብዓት አንጻር አሁንም አብዛኛው ከውጭ የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህን ለማስተካከል ለመድሃኒት ግብአት የሚውሉ በርካታ ጸጋዎችን ወደ ጥቅም መቀየር እንደሚገባ አንስተዋል።

በጥናትና ምርምር በመደገፍ ወደ ምርት ማስገባት እንደሚገባ ገልጸው፥ ኢንስቲቲዩቱ የምርምር ውጤቶች እና እውቀቶች ወደ ምርት እንዲገቡ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።


 

የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው የጥናት ውጤት የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ልማትን የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የካሳቫ ምርት ላይ የተደረገው የፋርማሲዩቲካል አዋጭነት ጥናት በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም ለሀገር እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸውን የምርምር  ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።


 

በጥናቱ አጠቃላይ የቢዝነስ ሁኔታ እና የገበያ ጥናት መደረጉን የገለጹት ደግሞ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ሽፈራው ሰለሞን ናቸው።

በዚህም በካሳቫ ምርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት አዋጭ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።

ጥናቱ ወደኢንቨስትመንት ሲገባ ከውጭ የሚገባውን ለመድሃኒት ግብዓት የሚያገለግል የካሳቫ ስታርችን በሀገር ውስጥ በመተካት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም