በመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት የእረፍት ጊዜያችንን አካላዊ ብቃትን በሚያጎለብቱ ስፖርቶች እንድናሳልፍ አስችለውናል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት የእረፍት ጊዜያችንን አካላዊ ብቃትን በሚያጎለብቱ ስፖርቶች እንድናሳልፍ አስችለውናል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 10/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት የእረፍት ጊዜያችንን አካላዊ ብቃትን ማጎልበት በሚያስችሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንድናሳልፍ አስችለውናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ታዳጊዎች ተናገሩ።
በየካና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች እንደ አዲስ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስጠት በጀመሩት አገልግሎት ዙሪያ ታዳጊዎችና የስፖርት ባለሞያዎች አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ታዳጊዎች መካከል አላዛር ሙሉጌታ እንደተናገረው ወደፊት የእግር ኳስ ተጫዋችነት ህልሙን እውን ለማድረግ እግር ኳስን የሚለማመድበት ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ አካባቢ ይቸገር እንደነበር አስታውሷል።
በተለይም 28 ሜዳ ተብሎ የሚጠራው ማዘውተሪያ በአዲስ መልክ ከመሰራቱ በፊት ቦታው አሸዋማ በመሆኑ እሱና ጓደኞቹ በስፖርት እንቅስቃሴ ወቅት ለጉዳት ተጋላጭ ነበርን ብሏል።
በመዲናዋ ለረጅም ጊዜያት ለስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ሆኖ መቆየቱ በእረፍት ጊዜው እራሱን በማይለውጡ አካባቢዎች ላይ ጊዜውን ሲያሳልፍ እንደነበረ የተናገረው ደግሞ ታዳጊ ብሩክ እዮብ ነው።
እግር ኳስን ለመጫወት ምቹ ባልሆነ ማዘውተሪያ ቦታ ልምምድ ሲያደርግ መቆየቱን የሚያስታውሰው ደግሞ በተለምዶ መላጣ ሜዳ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ያገኘነው ታዳጊ ቅዱስ ያሬድ ነው።
በአሁኑ ሰዓት መንግስት በአዲስ አበባ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ትኩረት መስጠቱ ስፖርታዊ ችሎታዎችን ለማሳደግ ምቹ እድል ፈጥሮልናል ብለዋል።
አሁን ላይ ትምህርት ቤቶች የተዘጉበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ታዳጊዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በማይጠቅም ነገር ከማሳለፍ ይልቅ ምቹ ሁኔታ በተፈጠረባቸው የስፖርት ማዘወትሪያ በመሄድ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማሳተፍ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
ሜዳዎቹ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውላቸው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸው ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አሰልጣኝ የሆነው ፍቅረስላሴ ይልማ፤ በአሁኑ ሰዓት እንደ ሀገር ታዳጊዎችን በስፖርቱ ዘርፍ ብቁ ዜጋ ለማድረግ መንግስት ያከናወናቸው ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በኮልፌ መላጣ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው የስፖርት ማዘውተሪያ ታዳጊዎችን በእግር ኳስ ስፖርት ለማብቃት በሚያደርገው እንቅስቃሴ አመቺ እንዳልነበር አንስቶ አሁን ላይ ችግሩ በመቀረፉ የተሻለ ስራ ለማከናወን እንዳነሳሳው ተናግሯል።
መንግስት ለታዳጊዎች የገነባቸው ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ በመሆናቸው በአግባቡ መያዝ ከኛ ይጠበቃል ያለው ደግሞ ሌላው በስፖርት አሰልጣኝነት ሞያ የተሰማራው ደምሰው ቦጋለ ነው።