በክልሉ እንደሀገር ተሞክሮ የሚሆኑ አበረታችሥራዎች እየተከናወኑ ነው - አቶ አደም ፋራህ

ሐረር፤ሐምሌ 10/2017 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል  እንደሀገር ተሞክሮ የሚሆኑ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ  ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ። 

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በሐረሪ ክልል በዘጠኙም ወረዳዎች የተገነቡ የፓርቲ ጽሕፈት ቤቶችን መርቀው ከፍተዋል።


 

በዚህ ወቅት  አቶ አደም ፋራህ፤  ከለውጡ ወዲህ በሐረሪ ክልል  ከፍተኛ እድገት መመዝገብ እንደተቻለ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ እንደሀገር ተሞክሮ የሚሆኑ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤  ለዚህም የአመራሩና የህዝብ አንድነት ወሳኝ ሚና እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል።

በዘጠኙም ወረዳዎች ወጪ ቆጣቢ መሰረት ባደረገ መልኩ የተገነቡ ህንፃዎች የፓርቲውን የፕሮጀክት አመራር ስርዓትን በተግባር የገለጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፤ እንደሀገር የተመዘገቡ ታላላቅ ድሎች የብልፅግና ፓርቲ ፖሊሲዎች ትክክለኛነትና ህዝባዊ ቅቡልነቶች ማሳያ መሆናቸውን አንስተዋል።

እንደ ክልልም አደጋ ውስጥ የነበረው በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ በመደመር እሳቤና በአመራር አንድነትና ቁጭት የተሰራውንም ጠቅሰዋል።


 

የሕዝቡ የልማት ጥያቄ በመመለስ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድም ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውና የኮሪደር ልማትም አበረታች መሆኑን አንስተዋል።

በምረቃ መርሃ ግብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመርን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና የክልል   ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም