የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለተግባር ተኮር የግብርና ትምህርት ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው- ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለተግባር ተኮር የግብርና ትምህርት ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው- ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)

ባሕርዳር፤ ሐምሌ 10/2017(ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት እየተሰጠ ላለው ተግባር ተኮር የግብርና ትምህርት ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች በባህር ዳር ከተማ ፋሲሎ 2ኛ ደረጃ እና መስከረም 16 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በትምህርት ቤቶች የሚከናወን የችግኝ ተከላ ስራ የአየርን ንብረት ሚዛንን ለመጠበቅ ከማገዝ ባለፈ ለምግብነትና ለውበት የሚሆን ነው።
በተለይ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት እየተሰጠ ላለው ተግባር ተኮር የግብርና ትምህርት በተሞክሮነት እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
በመሆኑም እንደቢሮ የተተከለው ችግኝ ፀድቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶችን አረንጓዴና ሳቢ ማድረግ የመማር ማስተማር ስራውን ማራኪና ተማሪዎች እንዲጓጉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ያሉት ደግሞ በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የቢሮው ባለሙያ ወይዘሮ ህብስቴ ካሴ ናቸው።
ከመትከለ ባለፈ መንከባከብና እንዲጸድቁ ማድረግ የክረምት ስራዎች አንዱ አካል እንደሆነ ገልጸዋል።
ሌላኛው የቢሮው ባለሙያ አቶ ጌታነህ መንግስት፤ በትምህርት ቤቶች የሚከናወን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የትምህርት ቤቶችን የምገባ መረሃ-ግብር ለማሳለጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አፕልና ማንጎን ጨምሮ ሌሎችም ለምግብነት ጭምር የሚያገለግሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዋናው ግብ እንዲጸድቁ ማስቻል መሆኑን አንስተው፤ ለዚህ ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ሰራተኛ የተከለውን ችግኝ የመከታተል ኃላፊነቱን መወጣት አለብን ብለዋል።