ደም ከመለገስ ባለፈ የለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ የድርሻችንን እንወጣለን-በጎፈቃደኛ ደም ለጋሾች - ኢዜአ አማርኛ
ደም ከመለገስ ባለፈ የለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ የድርሻችንን እንወጣለን-በጎፈቃደኛ ደም ለጋሾች
ወላይታ ሶዶ ፤ ሐምሌ 9/2017 (ኢዜአ)፦ደም ከመለገስ ባለፈ የደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ገለጹ።
በበጎ ፍቃድ ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በበጀት ዓመቱ 450ሺህ ዩኒት የሚጠጋ ደም መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ አገልግሎት ባንክ አስታውቋል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች መካከል ለ55 ጊዜ ደም የለገሰው አቶ ሰለሞን ኮታ የደም ልገሳ ተግባሩን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት እንደጀመረ ገልጿል።
በወቅቱ ለታመመ ጓደኛው ደም በመለገስ አገልግሎቱን መጀመሩን ገልጾ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የደም ልገሳ ተግባሩን በማጠናከር የሰው ህይወትን የመታደግ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግሯል።
ከእዚህ በተጨማሪ ሌሎችም ደም መለገስ ያለውን ፋይዳ አውቀው በደም ልገሳ ተግባር እንዲሳተፉ የማስገንዘብ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ድንገተኛ የልብ ቀዶ ሕክምና ባደረጉበት ወቅት በተለገሳቸው ደም ህይወታቸው መትረፉን የገለጹት ወይዘሮ የአለምነሽ ከበደ በበኩላቸው እሳቸውም ይህንን በጎ ተግባር ማስቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በተለያየ ምክንያት ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በየጊዜው ደም ከመለገስ ባለፈ ተሞክሯቸውን ለሌሎች በማካፈል የደም ለጋሾች ቁጥርን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የደም ባንክ አስተባባሪ ወይዘሮ ሶፊያ ይማም የደም ለጋሾችን ቁጥር ለመጨመር በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አበረታች ውጤት እየተገኘ መጥቷል ብለዋል።
በክልሉ በ2017 ዓ.ም 13 ሺህ 841 ዩኒት ደም ቢሰበሰብም ከጤና ተቋማት የደም ፍላጎት አንፃር አሁንም ቀሪ ስራዎች አሉ ያሉት ወይዘሮ ሶፊያ፣ የሚሰበሰበውን ደም መጠን ለማሳደግ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ማህበረሰቡ በደም ልገሳ ላይ ያለውን አመለካከት ለመቀየር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱንም ተናግረዋል።
የደም ባንክ አገልግሎት ማዕከላትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ ናቸው።
እንደኃላፊው ገለጻ በክልሉ በዓመት 90 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ የሚያስችል አቅም አለ።
ከዚህም አንጻር የዓመቱ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ይህን ለመቀየር ልዩ ዕቅድ በማውጣት በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ አገልግሎት ባንክ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ጤናዬ ደስታ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር ለማሳደግ በተሰራው ሥራ በበጀት ዓመቱ 450 ሺህ ዩኒት የሚጠጋ ደም መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በዚህም ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር እያደገ ቢመጣም ከሚያስፈልገው ደም አንጻር አነስተኛ በመሆኑ ስራውን ለማጠናከር ታቅዷል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ይህን ተረድቶ በበጎ ፈቃደኝነት ደም በመለገስ የሰውን ህይወት ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።