የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያው ተለዋዋጭ የኢኮኖሚ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገና የታክስ መሰረትን የሚያሰፋ ነው-ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2017 (ኢዜአ)፦ የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያው ተለዋዋጭ የኢኮኖሚ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገና የታክስ መሰረትን የሚያሰፋ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

 ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅን አፅድቋል።

በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ የማሻሻያ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የገቢ ግብር አዋጅ ዲጂታል ኢኮኖሚውን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዋጁ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ከዲጂታል ኢኮኖሚው ጋር የተጣጣመ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።


 

የታክስ መሰረትን በማስፋት የመንግስትን የገቢ መሰብሰብ አቅም ለማሳደግ እንዲሁም የታክስ ማጭበርበርን ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የማሻሻያ አዋጁን በተመለከተ ግልፅ ያልሆኑላቸውን ጉዳዮች በማንሳት፥ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ የማሻሻያ አዋጁ ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀ ጥናት እንደተደረገበትና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።

ተለዋዋጭ የሆነውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የገቢ ግብር እንደ ሀገር ለታቀደው የኢኮኖሚ እድገት እውን መሆኑ  ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዉ፣ ለዚህ ደግሞ አዋጁን ማሻሻል ተገቢና አስፈላጊ ነው ብለዋል።

መንግስት የዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋዮችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንና ከገቢ ግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚፈጥረው ጫና አለመኖሩንም አረጋግጠዋል።

የማሻሻያ አዋጁ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለማበረታታት፣ የታክስ ማጭበርበርን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጁን በአምስት ተቃውሞ፣ በ12 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ስብሰባው የስታርታፕ ረቂቅ አዋጅንም በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም