ቀጥታ፡

ማሻሻያ የተደረገበት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2017 (ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው ማሻሻያ የተደረገበትን የኢትዮጵያ የምርጫ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ አፅድቋል

በዚሁ አዋጅ 26 አንቀፆች እንደተሻሻሉ የተገለጸ ሲሆን፥ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚያስችል ተገልጿል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፥ የአዋጁን የማሻሻያ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

በዚሁ ጊዜ አዋጁ 7ኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊና ግልፅ በሆነ መልኩ ማካሄድ በሚያስችል መልኩ መሻሻሉን አንስተዋል።


 

ማሻሻያ ከተደረገባቸው አንቀፆች መካከል የሴቶችና አካል ጉዳተኞች የምርጫ ተሳትፎ፣ የቅሬታ አቀራረብ፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች የፋይናንስ ምንጭ፣ የቅሬታ አቀራረብና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ይገኙበታል ነው ያሉት።

እንደ ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢው ገለፃ፣ የተሻሻለው አዋጅ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የምርጫ ሥራን በተሻለ መልኩ መምራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።


 

ውስብስብ የሆነውን የምርጫ ሂደት በቴክኖሎጂ በማገዝ ግልፅ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ምርጫ ማካሄድ እንደሚያስችልም አንስተዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም የማሻሻያ አዋጁ ላይ ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸውን ሀሳቦች በመስጠት በሁለት ተቃውሞ፣ በአራት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቀውታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም