መንግስት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን አቅም ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው-ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን አቅም ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው-ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 10/2017 (ኢዜአ)፦መንግስት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን አቅም ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ለኢዜአ አመራሮች እና ሰራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመላው ኢትዮጵያ ወቅታዊ፣ ተገቢነት ያለው እና ተአማኒነት ያላቸውን መረጃዎች ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መጠናከር የኢትዮጵያ ሚዲያዎች መጠናከር ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህም ሚዲያዎች ተገቢነት ያለው፣ ደረጃውን የጠበቀ እና የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
መንግስት ጠንካራ ዜና አገልግሎት መኖር አለበት ብሎ እንደሚያምንና በዚህ ረገድም ኢዜአን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠንካራ የዜና አገልግሎት መኖር ለሀገር የሚዲያ ዘርፍ እድገት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢዜአ አቅሙን ለማጠናከር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።