ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመክፈቻ ቀን አራት ሜዳልያዎችን አግኝታለች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017 (ኢዜአ)፦ ሶስተኛው የአፍሪካ ከ20 እና 18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ማምሻውን በናይጄሪያ አቡካታ  ተጀምሯል።

በመክፈቻው የኢትዮጵያ አትሌቶች የተሳተፉባቸው አምስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል።

በ1500 ሜትር ሴት ከ18 ዓመት በታች ፍጻሜ ኤልሳቤጥ አማረ የብር፣ ደስታ ታደሰ የነሐስ ሜዳልያ አግኝተዋል።

አትሌት ትርሃስ ገብረህይወት በ3000 ሜትር ሴቶች ከ20 ዓመት በታች የፍጻሜ ውድድር የብር ሜዳልያ አግኝታለች።

እንዲሁም በ1500 ሜትር ወንድ ከ18 ዓመት በታች ሳሙኤል ገብረሃዋርያ የነሃስ ሜዳልያ  ለሀገሩ ማስገኘቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በስሉስ ዝላይ ሴት ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ኛቾክ ቾል፣ አትሌት ንብረት ክንዴ በ10000 ሜትር ወንድ ከ20 ዓመት በታች ፍፃሜ ደረጃ ውስጥ አልገቡም።

በአጠቃላይ በሻምፒዮናው መክፈቻ ኢትዮጵያ ሁለት ብር፣ ሁለት ነሐስ በድምሩ አራት ሜዳልያዎች አግኝታለች።

ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ 30 ወንድ እና 27 ሴቶች በድምሩ 57 አትሌቶችን ታሳትፋለች።

ሶስተኛው የአፍሪካ ከ20 እና 18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም