ልዩነትን ከግጭት በራቀ መልኩ በውይይት የመፍታት ባህል ሊዳብር ይገባል -የሀይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦ልዩነትን ከግጭት በራቀ መልኩ በውይይት የመፍታት ባህል ሊዳብር እንደሚገባ የሀይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

በኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት አስተባባሪነት የሀይማኖት አባቶች በትግራይ መቀሌ ያደረጉትን የሰላም ጥሪ በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሀይማኖት አባቶቹን በመወከል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ እንደገለፁት፣ የሀይማኖት አባቶቹ በቆይታቸው ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ እና አመራራቸው እንዲሁም ከክልሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል።


 

የሀይማኖት አባቶቹ ለባለድርሻ አካላቱ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።

የሀይማኖት አባቶቹ፣ በትግራይ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን ጠቅሰው፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፍታት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውንም አስረድተዋል።

ባለድርሻ አካላቱ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሚፈቱም ተስፋቸውን ገልፀዋል።

የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤም በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን በጎ አበርክቶ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሀጂ ኢብራሂም አመልክተው፣ ልዩነትን ከግጭት በራቀ አኳሃን በውይይት ብቻ የመፍታት ባህል በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ሊዳብር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም