የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በሚደረገው ጥረት የክልሎች የምርት አቅርቦት ትብብርና ትስስር ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በሚደረገው ጥረት የክልሎች የምርት አቅርቦት ትብብርና ትስስር ሊጠናከር ይገባል

ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በሚደረገው ጥረት የክልሎች የምርት አቅርቦት ትብብርና ትስስር ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለፁ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግስት እና በፓርቲ ትብብር የተከናወኑ አበይት ተግባራትን የሚገመግም መድረክ በድሬዳዋ ተካሂዷል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፤ በማጠቃለያ ንግግራቸው በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮችና መሰራት ስላለባቸው ቀጣይ አቅጣጫዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሀገርንና ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው በተለይም የኑሮ ውድነትን በማቃለል ረገድ በቀጣይ ብዙ ስራዎች ይጠበቃሉ ብለዋል።
በዚህ ረገድ ጅምሮቹ ጥሩ መሆናቸውን አንስተው እንደየ ክልሎቹ ነባራዊ ሁኔታ ምርቶችን በመለየትና አቅርቦትና ምርታማነትን በማሳለጥ በቀጣይም ብዙ መስራት ይገባል ብለዋል።
በምርት አቅርቦት ረገድ የክልሎች ትብብርና ጥብቅ ትስስር አስፈላጊ በመሆኑ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የቅዳሜ እና እሁድ ግብይቶችን ጨምሮ ለገበያ ማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው የኮንትሮባንድ ንግድንና የገበያ አሻጥሮችን በጥብቅ በመከታተል ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታትም በቅንጅት መስራት ይገባልም ብለዋል።
የድሃ ተኮር ፕሮግራሞችን አጠናክሮ መቀጠል፣ የአመጋገብ ባህል እንዲሻሻል መጣርና የምርት አማራጮችን ማስፋትም እንዲሁ።
ከስራ እድል ፈጠራ አንፃር መልካም ጅምሮች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ አደም የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥልቀት በማየት በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም የብድር ሁኔታን የማመቻቸት፣ የስልጠና እድሎችን የማስፋትና የሰዎች የአስተሳሰብ በመለወጥ ረገድ እንዲሁም የስራ እና የመሸጫ ቦታዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አመራሩ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከተረጅነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ከቤተሰብ እቅድ ጀምሮ የድጋፍና ክትትል ስራን በማጠናከር ከሌማት ትሩፋትና ሌሎች የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ኢኒሸቲቮች ትግበራ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲፈጠር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል አቶ አደም።
የሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠትና ዘላቂ መፍትሄ ለመሻትም የመጠባበቂያ ክምችትን ማሳደግና ጠንካራ የአሰራር ስርአት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በጥንቃቄ በመለየት ለፈጣን ምላሽ፣ በቂና የተሟላ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።