አረንጓዴ አሻራ ምቹ፣ ውብና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሀገርን ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ተግባር ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እያካሄደችው የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ምቹ፣ ውብና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የማይበገር ሀገርን ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ተግባር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል። 

በዚህም የተለያዩ ተቋማትና ህብረተሰብ ክፍሎች በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች አሻራቸውን በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ።

ዛሬ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አመራር አባላትና ሰራተኞች፣ ከፌዴራል ስፖርት ማህበራት፣ ከኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት አመራር አባላትና ሰራተኞች ጋር በመተባበር በገላን ስታዲዬም የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምቹና ውብ አካባቢን በመፍጠር ለመጪው ትውልድ  ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የማይበገር ሀገርን የማስረከብ ተግባር ነው።  

ይህንን እውን ለማድረግ ወጣቱ  እያደረገ ያለውን አበርክቶና ተነሳሽነት አድንቀዋል፡፡ 


 

ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ የተሰሩ ስራዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል እየሆኑ መምጣታቸውን የተናገሩት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ ናቸው።


 

 ይህም ዛሬ በተግባር የታየበት መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም  የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው የታለመው አላማ እንዲሳካ እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው እንደገለጹት ፌዴሬሽኑ ለአረንጓዴ አሻራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።


 

የሸገር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ናስር ሁሴን፤ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ችግኞችን መትከል ስፖርተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ባህል እንዲያደርጉና እንዲንከባከቡ ለማስቻል ነው ብለዋል።  


 

ከተሳታፊዎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ከፍለ ከተማ ወረዳ 13 ነዋሪ ወጣት በድሉ በቀለ እና በሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ቡሳሞ ሞንደ እንዳሉት በየዓመቱ በሚካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ አሻራቸውን እያኖሩ ነው።


 


 

ችግኞችን መትከልና እስከ ጽድቀታቸው ድረስ መንከባከብ ከሁሉም ሰው የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም