ከ6 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎችን ወደ ስራ የሚያስገቡ የተለያዩ ክህሎት መር ስልጠናዎችን መስጠት ተችሏል-ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
ከ6 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎችን ወደ ስራ የሚያስገቡ የተለያዩ ክህሎት መር ስልጠናዎችን መስጠት ተችሏል-ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ከ6 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎችን ወደ ስራ የሚያስገቡ የተለያዩ ክህሎት መር ስልጠናዎችን መስጠት መቻሉን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግስት እና በፓርቲ ትብብር የተከናወኑ አበይት ተግባራትን የሚገመግም መድረክ በድሬዳዋ ተካሂዷል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የብልፅግና ፓርቲ ዋና መስሪያ ቤት እና የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አመራሮች፣ ሚኒስትሮች እና የየክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ከተረጅነት የመውጣት ጥረት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የገበያ ማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ረገድና ሌሎችም ጉዳዮችን በመዳሰስ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትና የተመዘገቡ ውጤቶችን በተመለከተ በመድረኩ በስፋት ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፤ በተጠናቀቀው በጀት አመት የዜጎችን የስራ ፍላጎትና ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ውጤትም ተመዝግቧል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ6 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎችን ወደ ስራ የሚያስገቡ የተለያዩ ክህሎት መር ስልጠናዎችን መስጠት መቻሉንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ4.5 ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች ክህሎት መር የስራ ዕድል በሀገር ውስጥና በውጭ የስራ ዕድል እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቅሰው በሀገር ውስጥ የተፈጠረው የስራ ዕድል ከተያዘው ዕቅድ በላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ(ዶ/ር)፤ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ የሀገሪቷን ዘርፈ ብዙ ልማትና እድገት ማሳለጥ መቻሉን አንስተዋል።
የገበያ ንረትን እና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድም በስፋት መሰራቱንና ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፣ በከተማዋ የሚስተዋሉ ማህበራዊና የምጣኔ ሃብት ችግሮችን ለማቃለል በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ31 ሺህ በላይ ዜጎች ባሉ ፀጋዎች ተጠቅመውና በተመቻቸላቸው መደላድሎች ታግዘው ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።