በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ በጣለው ከባድ ዝናብ ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ በጣለው ከባድ ዝናብ ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ እየተደረገ ነው

አፋር፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ በጣለው ከባድ ዝናብ ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሸን አስታወቀ፡፡
በክልሉ በትናንትናው እለት ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሎጀስቲክስ ኦፕሬሽን ምክትል ዳይሬክተር አሊ መሀመድ፤ ክስተቱን በማስመልከት ለኢዜአ መረጃ ሰጥተዋል።
በክልሉ አፍዴራ ወረዳ በትናንትናው እለት ነፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱንና ብዙዎችን ማፈናቀሉንም ተናግረዋል።
በአደጋው ምክንያት በ32 ሰዎች ላይ ከባድ እንዲሁም በ22 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰው፤ ተጎጂዎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በአደጋው ከ2 ሺህ 500 በላይ ቤቶች መፍረሳቸውን አንስተው ፤ አምስት የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሰዋል።
ክስተቱን ተከትሎ ለተፈናቀሉ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ፣ አልባሳትና የፍራሽ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው፤ ቀጣይነት ያለው እገዛና ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ለአደጋው አስቸኳይ ምላሽ የሚሰጥ ከተለያዩ አካላት የተዋቀረ ግብረ ሃይል መቋቋሙን ተናግረው ፤ ቅንጅታዊ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከወረዳው አስተዳደር፣ ከጸጥታ ሃይል፣ በየደረጃው ካለው አመራርና አጠቃላይ ህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።