ሆስፒታሉ ሕክምና ለማግኘት ርቀን ስንሄድ ሲደርስብን የነበረውን እንግልትና ወጪ አስቀርቶልናል-ተገልጋዮች

ቦንጋ፤ ሐምሌ 9/2017(ኢዜአ)፦በአካባቢያቸው የተገነባው ቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል  ሕክምና ለማግኘት ርቀው ሲሄዱ ይደርስባቸው የነበረን እንግልትና ከፍተኛ ወጪ ማስቀረቱን ተገልጋዮች ገለጹ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

በወረዳው የቆንዳ ከተማ ነዋሪ ገዋተራሻ መሸሻ ከዚህ ቀደም በአቅራቢያቸው ሆስፒታል ባለመኖሩ ከፍ ያለ ሕክምና ለማግኘት ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው ስለሚጓዙ ለወጪና ለእንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው ቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ይህን ችግር በመፍታት በቅርበት የተሻለ የጤና አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።

ቀደም ሲል በአካባቢያቸው የተሟላ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ባለመኖሩ በተለይ በእናቶችና ሕጻናት ላይ ጉዳት ይደርስ እንደነበር ያስታወሱት ሌላው የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ነቢላ አባፎጊ፣ የሆስፒታሉ መመረቅ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ እፎይታ መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

ሆስፒታሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ ድካምና ወጪን ከማስቀረት ባለፈ ፍትሃዊ የጤና ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥም ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ አዋላጅ ነርስ የሆኑት ሲስተር መሠረት መንገሻ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በጤና ጣቢያ የተሟላ አገልግሎት ስላልነበር በተለይ ነፍሰጡር እናቶችን ወደ ቦንጋና ጅማ ከተማ ሆስፒታሎች በሪፈር ለመላክ ይገደዱ እንደነበረ አስታውሰዋል።


 

የተመረቀው ሆስፒታል አስፈላጊ ግብአቶች ተሟልቶለት በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ ያለው ጥረት የብዙዎችን ሕይወት ከመታደግ ባለፈ እንግልትን ያስቀራል ብለዋል። 

በወረዳው ሆስፒታል ባለመኖሩ ህብረተሰቡ ተገቢውን የጤና አገልግሎት እያገኘ እንዳልነበር የገለጹት ደግሞ የገዋታ ወረዳ  ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱ አባግዲ፣ "አሁን የተመረቀው ሆስፒታል ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሽለዋል" ብለዋል።


 

በቀን ቢያንስ ሦስት እናቶች ወደ ቦንጋና ጅማ ሆስፒታል በሪፈር እንደሚላኩ አስታውሰው፣ ይህም ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ ይዳርጋቸው እንደነበር አመልክተዋል።

ለአገልግሎት የበቃው ሆስፒታል ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጥ በወረዳው በኩል አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው እንዳሉት፣ የጤና ተቋማትን የማስፋፋትና አገልግሎት አሰጣጣቸውን የማሻሻል ሥራ እየተሰራ ይገኛል።


 

ይህም የህብረተሰቡን የጤና ተጠቃሚነት  እያሳደገው መሆኑን ገልፀው፣ የተመረቀው የቆንዳ ሆስፒታልም የእዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ወደአገልግሎት እንዲገባ አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲሟሉ ይደረጋል ያሉት ሃላፊው፣ የአካባቢው ማህበረሰብም ተቋሙን በባለቤትነት በመደገፍ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቅርቡ በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ የተገነባውን የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም